የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ግ.ት.ኤ.) ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በ8028 የአርሶአደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመሩ ላይ የእንስሳት ምክር እና የኮቪድ-19 ጤና ምክር ይዘቶችን በማካተት ማሰራጨት ጀመረ። እነዚህን አዲስ ይዘቶች በአሁኑ ወቅት በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ወላይትኛ እና ሲዳምኛ) ማግኘት ይቻላል።

ከተባበሩት መንግስታት የምግብ እና ግብርና ተቋም የተገኘው መረጃ (የተ.መ.ድ. የምግብ እና ግብርና ተቋም፣ እ.ኤ.አ. 2018) እንደሚጠቁመው ከሆነ 1.3 ቢሊዮን ህዝብ የገቢ ምንጩን የሚያገኘው ከእንስሳት ዘርፍ ከመሆኑም በላይ ከዓለም አቀፍ የግብርና ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ውስጥ 40 በመቶውን አስተዋጽኦ የሚያደርገውም ይኸው ዘርፍ ነው። የኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት በአፍሪካ ትልቅ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ሲሆን ከሞላ ጎደል ከሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 20 በመቶውን እንዲሁም ከሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ 15 በመቶውን አስተዋጽኦ ያደርጋል (የተ.መ.ድ. የምግብ እና ግብርና ተቋም፣ እ.ኤ.አ. 2019)። የእንስሳት ንዑስ ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በገጠር ከሚኖረው ህዝብ ውስጥ የ80 በመቶውን ኑሮ ይደግፋል።

“በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ቦታ የሚገኙ አርሶአደሮች የሚገኙበት ስፍራ የትም ይሁን የት መረጃን መሰረት በማድረግ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ቁልፍ እና ጠቃሚ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት መቻል አለባቸው። በተጨማሪም ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ማህበረሰባቸውን ከበሽታው መከላከል እንዲችሉ በአሁኑ ወቅት ዓለምን እየፈተነ ስለሚገኘው ወረርሽኝ ወቅታዊ መረጃዎችን ሊያገኙ ይገባል። በመሆኑም 8028 የአርሶ አደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመርን በመጠቀም ወሳኝ እና ወቅታዊ የእንስሳት እና የኮቪድ-19 መረጃዎችን በቀላሉ ሊያገኟቸው በሚችሉበት መልኩ አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶአደሮቻችን ለማድረስ ከአጋሮቻችን ጋር በጋራ ለመሥራት ወስነናል።” ብለዋል የግ.ት.ኤ. ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሊድ ቦምባ።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ “እንስሳት ለኑሮ/ለገቢ፣ ለቤተሰብ ስነ-ምግብ፣ ለሥራ ዕድል እንዲሁም ለሌሎች ማህበራዊ ግዴታዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ዋነኛ ሀብቶች ውስጥ አንዱ ነው። በተጨማሪም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። በመሆኑም አነስተኛ ይዞታ ላላቸው እንስሳት አርቢዎች በተሻሻሉ የአመራረት እና የሥራ አመራር አሠራሮች እንዲሁም በኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎች ዙሪያ አስፈላጊውን ወቅታዊ መረጃ መስጠት በከፍተኛ ሁኔታ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ነው አርሶአደሮች በአሁኑ ወቅት ካለው ወረርሽኝ ራሳቸውን ከመጠበቅ ጎን ለጎን ተገቢውን የምክር አገልግሎት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራት የጀመርነው” ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የ8028 የአርሶ አደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመር  አገልግሎትን በመጠቀም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ሰብል አምራች አርሶ አደሮችን ለመደገፍ በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሁልጊዜም አጋራችን ሆኖ ቆይቷል። እስከ አሁን ድረስ 8028 የአርሶ አደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመር  ወደ 46.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ጥሪዎችን ከአርሶአደሮች ተቀብሎ ያስተናገደ ሲሆን ለዚህም አገልግሎቱን ከክፍያ ነጻ ያቀረበውም ኢትዮ ቴልኮም ነው።

እንስሳትን የሚመለተው 8028 የአርሶአደሮች የግብርና መረጃ መስመር  በሚከተሉት አራት ዋና ዋና የእንስሳት ምድቦች አስፈላጊውን የምክር አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረ ተጨማሪ አገልግሎት ነው፡- የእንስሳት ተዋጽኦ፣ ማደለብ (ከብት እንዲሁም በግ እና ፍየል)፣ የንብ እርባታ፣ የዶሮ እርባታ (አነስተኛ የንግድ የዶሮ እርባታ እና የተሻሻለ የቤት ውስጥ የዶሮ እርባታ)። በተጨማሪም የምክር አገልግሎቱ በመኖ ሀብት አመራረት እና አጠቃቀም ዙሪያ የተሻሻለ የሥራ አመራር እና አሠራር ያሏቸው ቴክኖሎጂዎችን አቀባበል እና የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ለዚሁ ዓላማ በተመደቡ የኤክስቴንሽን ሰራተኞች በሚደረግ ሰርቶ ማሳያ እና ተሳትፎ አማካኝነት ይበልጥ የሚያቀል ሲሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ግን ይህን ማድረግ ከባድ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት ያለው ወረርሽኝ ያስከተላቸውን ተግዳሮቶች በማገናዘብ ግ.ት.ኤ. ከመርሲ ኮርፕስ ኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለ8028 የአርሶአደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመር  ሲስተም ተጠቃሚዎች በኮቪድ-19 ዙሪያ አሳታፊ የድምጽ ምልልስ (IVR) አገልግሎት ጀምሯል። በመሆኑም አሁን አርሶ አደሮች ደህንነቱ በተጠበቀ አስተራረስ፣ በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ግንኙነት፣ በኮቪድ-19 የተነሳ የሚመጣ ሞትን በማስተናገድ እና ግንኙነት ባላቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች ላይ ያተኮረ የኮቪድ-19 የጤና ምክር ማግኘት ይችላሉ።

የመርሲ ኮርፕስ የግብርና ፋይናንስ (AgriFin) ፕሮግራም የበረሀ አንበጣ እና የኮቪድ-19 ድንገተኛ ሁኔታ ሥራ አመራር እና የአየር ንብረትን ያገናዘበ ዲጂታል ግብርና ኃላፊ የሆኑት ጆን መንዲ “አብዛኛውን ጊዜ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶአደሮች ያሉባቸውን የኮቪድ-19 መረጃ ክፍተቶች በመሙላት ረገድ ዲጂታል የመገናኛ ዘዴዎች ወሳኝ ሚናን ሲጫወቱ ቆይተዋል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የራስን ጤና የመጠበቂያ እንዲሁም ማህበረሰቡን ከኮቪድ-19 የመከላከያ ምርጥ ዘዴዎችን ለማድረስ ከግ.ት.ኤ. 8028 የአርሶአደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመር ፕሮጀክት ቡድን ጋር በጋራ መሥራት ጀምረናል” በማለት አብራርተዋል። ይህ አገልግሎት መጀመሩ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎቶች እና መገልገያዎች እጥረት ባለባቸው የገጠር አካባቢዎች የሚኖረው ጥቅም ወሳኝ ነው። በተጨማሪም በሩቅ ቦታዎች ለሚገኙ አርሶአደሮች በተለይም ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በአካል መገኘት ሳያስፈልግ የጤና ትምህርቶችን ለመስጠት የሚያስችል ቀልጣፋ ዘዴ ነው።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ግ.ት.ኤ.) 8028 ግብርና ነክ የምክር አገልግሎት አሳታፊ የድምጽ ምልልስ/አጭር የጽሁፍ መልዕክት (IVR/SMS) አገልግሎትን መስጠት የጀመረው ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደ/ህ/ብ/ብ እና በትግራይ ክልል በሚገኙ 21 ወረዳዎች ውስጥ ለአምስት ወራት የቆየ የሙከራ ትግበራ ካከናወነ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. ነበር። ከዚያም በኋላ አገልግሎቱ ለስድስት ዓመታት ሳይቋረጥ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በዚህም የ8028 የአርሶአደሮች ነፃ የግብርና መረጃ መስመር እና የድጋፍ ዴስክ ሥርዓት ተጠቃሚዎች በአገዳ እህሎች፣ በጥራጥሬ እና በቅባት እህሎች ዙሪያ ያሉ 21 የሰብል ዓይነቶችን እንዲሁም የቤተሰብ መስኖ ሰብሎችን በተመለከተ በተለያዩ የግብርና እንቅስቃሴዎች ዙሪያ እያንዳንዳቸው እስከአምስት ደቂቃ ድረስ ርዝመት ባላቸው ይዘቶች አማካኝነት መረጃዎችን ሲያገኙ ቆይተዋል።

Facebook
Twitter
LinkedIn