አዲስ አበባ መስከረም 7 2013 – የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ግትኤ) ከሜርሲ ኮርፕስ እና ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት ያዘጋጁትን ለበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ መረጃ መስጫነት የሚያገለግል የዋትስአፕ መተግበሪያ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህ የመረጃ አገልግሎት መስመር የኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊ በሆነው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ዙሪያ እያከናወነ ለሚገኘው  መረጃዎችን የመሰብሰብ አገልግሎትና የቅኝት ስራዎችን ለማገዝ የተዘጋጀ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የምግብና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) እንደሚለው፣ አሁን ባለው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ፣ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ እና በስፋት በተሰራጨው የበረሃ አንበጣ መንጋ ምክንያት የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያልተጠበቀ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ስጋት አጋጥሟል፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ2011 እና 2012 ዓ.ም. አጋማሽ መካከል የነበረው ምቹ የአየር ሁኔታ እና ምርት  የበረሃ አንበጣ  መንጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲባባስ አስተዋፅኦ አድርጓል ፡፡ የበረሃ አንበጣው  በብዙ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በከፍተኛ ደረጃ  በሰብሎች  እና የግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን  ይህም ከ25 ዓመት በኋላ የታየ ነው ብሎታል፡፡

የግትኤ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ ካሊድ ቦምባ እንዳሉት ‹‹በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የበረሃ አንበጣ መንጋ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በዋናነት አርሶአደሩን የጎዳው ስለመንጋው ያለው የመረጃ እጥረት ነው ፤ ለዚህም ነው ከአጋሮቻችን ጋር ለመተባበር እና አርሶአደሩ ማግኘት የሚገባውን አዳዲስ መረጃዎች በቀላሉ ሊያገኝ እና ሊጠቀምበት የሚችልበትን መንገድ ለመዘርጋት የወሰንነው፡፡››

የግብርና ሚኒስቴር ደኤታ የሆኑት ክቡር ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ ‹‹የበረሃ አንበጣ በዓለም ላይ ከቦታ ቦታ በከፍተኛ ብዛት ከሚፈልሱና ከሚዘዋወሩ ነፍሳት የሚጠቀስ ሲሆን እኛም አንድ ዓመት በቀረበ ጊዜ ውስጥ ባልተጠበቀ ፍጥነት የሚሰራጭ መሆኑንም  ለማየት ችለናል ፡፡ ስለሆነም ይህንን በፍጥነት የሚዛመት መንጋ አሁን ከፈጠረው ከፍተኛ ስጋት በላይ ከመሆኑ በፊት ለመዋጋት ሰፊ የመሳሪያ እና የግብዓት ዝግጅት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል

በአሁኑ ጊዜ የበረሃ አንበጣ ስለመከሰቱ ፣ ተፈጥሯዊ ባሕሪና እንቅስቃሴያቸው ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎች በዋትስአፕ የመረጃ መስመር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ይህ መረጃ  በግትኤ  8028  የመረጃ መስመር  ለተመዘገቡና ከ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶአደሮች በድምፅ እና በፅሁፍ ይደርሳቸዋል፡፡ 8028 የመረጃ መስመር መልዕክት ከማስተላለፍም ባሻገር በበረሃ አንበጣ ክስተት ዙሪያ 11 ሺህ የልማት ኤጀንሲዎች እና 600 የግብርና ባለሙያዎችን ፣በማካተት በሳምንት አራት ጊዜ በሚደረግ አጭር የፅሁፍ መልዕክት መሰረት በአራት የኢትዮጵያ ክልሎች እየተሰራ ላላ የዳሰሳ ጥናት  ስራ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል ፡፡

በኢትዮጵያ የሜርሲ ኮርፕስ ዳይሬክተር  አቶ መላኩ ይርጋ በበኩላቸው እንዳሉት ‹‹ ይህ ጅምር ባለድርሻ አካላት የበረሃ አንበጣ መንጋን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በማወቅ ለመከታተልና ለመተንበይ የሚያስችል ጠቃሚ መረጃዎች እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም  ፖሊሲዎችን ለመቅረፅ ያግዛል፤›› ጨምረውም ‹‹እነዚህን መረጃዎች ለማድረስ መቻል ከፊት የተደቀነን አደጋ ከመከላከል አልፎ ሰዎች ከአካባቢያቸው እና ካላቸው የተፈጥሮ ሃብት ጋር ጥብቅ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ያሏቸውን መልካም አጋጣሚዎች መጠቀም እንዲችሉ፣ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን በጋራ ለመቋቋም እንዲችሉ ይረዳል፡፡›› ብለዋል

የመረጃ መስመሩ ቀድመው የተዘጋጁ ስለ በረሃ አንበጣ የሚገልጹ መሠረታዊ መረጃዎችን የያዘ ሲሆን አዳዲስ ምልከታዎችን እና መረጃዎችን ጨምሮ የመንጋው ወረራ ባጋጠመ ጊዜ በመከላከሉ ሂደት ላይ ምን መደረግ እንዳለበት እና እንደሌለበት ያቀርባል፡፡ መረጃዎቹ ከፍተኛ ሽፋን በመስጠት በእጅ እና በዘመናዊ መንገድ  የተሰበሰቡት ዘር በሚዘራበት ወቅት ነው፡፡  የተሰበሰቡት መረጃዎች ፣ ከተለያዩ የሙያ መስክ ማለትም ከአግሮኖሚ፣ ባዮሎጂ፣ ኢንቶሞሎጂ፣ ሜትሪዮሎጂ፣ ኮምፒውተር ሳይንስ፣ እና ቴሌኮሙኒኬሽን የተወጣጡ ባለሙያዎችንና በአካባቢ ላይ ለሚደረግ ምርምር የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን የተጠቀመ ሲሆን በዚህ ደረጃ በቅንጅት በመሰራቱም  መረጃውን  በአግባቡ በመመርመር ለመተንተንና ጠቃሚ መረጃዎችን ለማውጣት እንዲቻል አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ የዋትስአፕ የመረጃ መስመርን የዋትስ አፕ መተግበሪያን ተጠቅሞ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት  ወደ +251 95 287 8787   ላይ ‘‘Locust’ ‘Laqin’ ‘Ayaxa’ ‘Hawaannisa’ ‘ኣንበጣ’ ‘አንበጣ’, ብሎ በመላክ መረጃውን ማግኘት ይቻላል፡፡ አጋሮቻችን  ይህ መንገድ በአነስተኛ ወጪ የገጠሩን  ማህበረሰብ፣ የአንበጣ መረጃዎችን በሚፈለገው ልክ ለማድረስ የሚያስችል እጅግ ጠቃሚ ዘዴ በማለት አወድሰውታል፡፡

የዚህ የዋትስአፕ የመረጃ መስመር መጀመር የአርሶአደሩን እና የኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ግንዛቤ ለመጨመር፣ እንዲሁም በቀረበላቸው የአጭር የፅሁፍ መልዕክት እና የዋትስአፕ የመረጃ መስመር መረጃዎችን በመካከላቸው የመለዋወጥ ልምድ እንዲዳብር በማድረግ ከፍ ሲልም በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እንዲሁም እንቅስቃሴ በተገደበበት ወቅት  ያጋጠመውን ፈተና ለማለፍ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ያላቸውን ከፍተኛ ሚና  እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡

የአንበጣ መንጋ፣ ሊከሰት የሚችልበት አቅጣጫ፣ አማካኝ የዕድሜው ግምት፣ አማካኝ የመራቢያ ቀን የመሳሰሉትን  መረጃዎችን ለማግኘት ፍላጎት ያለው ማንኛውም ግለሰብ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን መገናኛ በመጫን መረጃዎቹን ማግኘት ይችላል፡፡

https://pennstate.maps.arcgis.com/apps/opsdashboard/index.html#/121dd23b5e264e25a685b57f40042899

እንደ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የግብርና ድርጅት መረጃ ፣ የበረሃ አንበጣ መንጋ በአሁን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በጅግጅጋ፣ ሃረር፣ ድሬዳዋ እና የጅቡቲ ጠረፍ ላይ ተሰራጭቶ ይገኛል፤ በተጨማሪም ከየመን የመጣ በርካታ የአንበጣ መንጋ በአፋር ክልል ተከስቷል፡፡ የተገኘው በቂ ዝናብ ሰፋፊ አረንጓዴ ቦታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሲሆን ይህ አጋጣሚም ለመንጋው ምቾት ፈጥሮ በነሐሴ እና መስከረም ወር ላይ  የአንበጣ ወረርሽኝ እንደ አዲስ እንዲስፋፋ ምክንያት ሊሆን ይችላል  ተብሎም ይገመታል፡፡ ይህ አዲስ የተጀመረው የዋትስአፕ መተግበሪያ የመረጃ መስመር ከሌሎች ዲጂታል ዘመናዊ መሳሪያዎች ጋር በመጣመር የኢትዮጵያ መንግስት የአንበጣ መንጋውን በተሳካ ሁኔታ ለመከታተል፣ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል እንዲችል ያግዘዋል ተብሎ ይታመናል ፡፡

Facebook
Twitter
LinkedIn