የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርና ሚኒሰቴር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ከ175 በላይ የሚሆኑ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከላትን በ4 ክልሎች ((በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ.ብ.ብ.ህ እና ትግራይ) በማቋቋምና በማስፋፋት አርሶ አደሮች አቅርቦት በአንድ መስኮት ከባለሙያ አገልግሎት ጋር እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ የግብርና ግብዓት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የታወቀ ነዉ፡፡ ነገር ግን የግብርና ግብዓት በሚፈለገዉ መጠንና ጥራት፣ በወቅቱ፣ በተጠያቂነትና ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ያለመቅረብ ለዘመናት እንደ ችግር ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዘህ ጋር ተያይዞም ስለግብዓቱም በቂ መረጃ ያለመኖር፣ እንዲሁም ግብዓቶች በተበታተነ መንገድ በተለያዩ ድርጅቶች መቅረባቸዉ አርሶ/አርብቶ አደሩ በሙሉ ልብ ገዝቶ መጠቀም አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ምንም እንኳን አገራችን ለግብርና እጅግ በጣም ተስማሚ ብትሆንም በዚያዉ ልክ ከሚፈለገዉ የምርትና ምርታማነት ዕድገት ደረጃ መድረስ አልተቻለም፡ ፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና አገልግሎት ማዕከላት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ2008 እስከ 2010 ዓ∙ም በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ የተገኘዉም ዉጤት እጅግ በጣም አበረታች በመሆኑ ከ2011 ጀምሮ ማዕከላቱን በየወረዳዎች የማቋቋም፣ ተሞክሮዎችንም በማስፋፋትና በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ሁሉም የግብርና ግብዓቶች (ዘር፣ አግሮ ኬሚካል፣ የእንስሳት ህክምና መድሃኒት፣ መኖ፣ የእርሻ መሳሪያዎች … ወዘተ) በጥራት፣ በሚፈለገዉ መጠን፣ ጊዜ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ማዕከል ዉስጥ ለተጠቃሚዉ ተደራሽ ማድረግ ነዉ፡፡ ከዘህ በተጨማሪም አገልግሎቱም በዕዉቀት ላይ የተመሰረተ ሆኖ እያንዳንዱ ተጠቃሚ ግዥ ከመፈፀሙ በፊት ስለግብዓቱ በቂ መረጃና ዕዉቀት ከማዕከሉ ሙያተኞች እንዲያገኝ የሚያስችል ነዉ፡፡ በተጨማሪም ማዕከላት በአካባቢያቸዉ ለሚገኙ ማህበረሰብ የስልጠና፣ የመስክ ሰርቶ ማሳያ እና ሌሎች የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለመስጠት ታሰቦ የተደራጁ ናቸዉ፡፡ ፕሮጀክቱ በሞዴልነት ከተጀመረበት ከ2008 እስከ ዛሬ ድረስ ከ170 ማዕከላት በላይ በተጠቀሱት ክልሎች ተመርቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን በዚህም በሚሊየኖች ብር የሚቆጠር መጠን ያላቸው ደረጃቸውን የጠበቁ ግበዓቶች ለአርሶአደሮች ማቅረብ ችለዋል፡፡ አርሶ አደሮችም እርካታቸውን በስፋት ገልጸዋል፡፡ በአርሶ አደሮች ዘንድ ይታይ የነበረዉን ክፍተት ከመሙላት አንጻር እጅግ አበረታች ውጤት በመታየት ላይ ነዉ፡ ለምሳሌም ያህል በ2013 ዓ∙ም ግማሽ ዓመት ማዕከላቱ ከ390 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያየ የግብርና ግብዓትን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ/አርብቶ አደሮች ማቅረብ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሙያተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እንዲሁም ከ5000 በላይ አርሶ/አርብቶ አደሮችና የመንግስት ሙያተኞች በማዕከላቱ ስልጠና አግኝተዋል፡፡ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና በአንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌም አርሶ/አርብቶ አደሮች ሁሉንም ጥራታቸው የተረጋገጠ የግብዓት ዓይነቶችን በአንድ መስኮት በማንኛዉም ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋና ከባለሙያ ምክር ጋር ማግኘት ማስቻሉ ተጠቃሽ ነዉ፡፡ ከዘህ በተጨማርም ለመንግስትም የግብዓትን ዱካና ስርጭትን መከታተል ማስቻሉ፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩ፣ ወረዳ ላይ በተለይ በግብርና ላይ የግል ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ማድረጉና ለድጋፍ፣ ክትትል እና ተጠያቂነትን ለመፍጠር መቻሉ ሊጠቀሱ የሚችሉ ዋና ዋና ተሞክሮዋች ናቸዉ፡ ፡ ከላይ እንደተጠቀሰዉ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከል በሙከራ ከ20 ማዕከላት በመነሳት ዛሬ ከ170 ማዕከላት በላይ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ እንደ ግብም አንድ ማዕከል በእያንዳንዱ የግብርና ኮመርሻላይዜሽን ክላስተር ወረዳ ለማቋቋም ታስቦ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በላይ የተጠቀሰዉ ዉጤት እንዲመዘገብ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና የማቴሪያል ድጋፍ አድርጓል፡፡ ለምሳሌም በቅድሚያ ደረጃዉን የጠበቀ የማዕከል ሕንፃ ዲዛይን በማሰራትና እንዲፀድቅ በማድረግ፣ የእንዳንዱን ማዕከል በዉስጥ ቁሳቁስ እንዲሟላ ማድረግ፣ የሙያተኞች ቅጥር እንዲፈፀምና እሰከ አንድ ዓመት ድረስ ደመዎዝ ክፍያ መፈፀም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚካሄዱ የማህበረሰብ ስልጠና፣ ሰርቶ ማሳያና መስክ ጉብኝት ወጭዎችን ሙሉ በሙሉ መሸፈን፣ የማዕከሉ ሙያተኞች ተደጋጋሚ የሙያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙና የዛሬዉ ዓይነት የመሰለ ጤናማ የሆነ የንግድ ትስስር መፍጠሪያ መድረኮችን ማመቻቸት የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡ ማዕከላት የሚጠበቅባቸዉን ተግባር እና አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ተግዳሮቶችን በጋራ እንዲፈቱ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌም እያደገ የመጣውን የአርሶ/አርብቶ አደሮችን ፍላጎት ለማሟላት ሁሉንም ግብዓቶች በበቂ መጠን ከአስመጭዎች ወይም ከአከፋፋዮች በአስተማማኝ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሰዉ ሰራሽ ዕጥረት መቆጣጠርን፣ ፍትሃዊ ግብይትን እንዲፈጠር እና ተያያዥ ችግሮችን መፍታት ለዘላቂነታቸዉ ወሳኝ ነዉ፡፡ የዚህ ዉይይት መድረክ ዓላማ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከላይ የተቀመጠዉን ግብ ለመድረስ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

Facebook
Twitter
LinkedIn