የኢትዮጵያ አስደናቂ ምድር፣ በውብ ተፈጥሮ እና ያልተነካ እምቅ ሃብት የታደለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ሁሉ መጠቀም እራሷን ካለችበት የድህነት አዘቅት ለመውጣት ብትችልም  ዓለምአቀፍ የግብርና ትስስር ማጣት እና አምራቹን እና ገበያውን የሚያገናኙ መድረኮች ባለመኖራቸው ካለችበት እንዳትንቀሳቀስ እና አቅሟን በበቂ ሁኔታ እንዳትጠቀም ይዘዋት ቆይቷል፡፡

ይህ ሁኔታ ግን ከአስር ዓመት በፊት የኢትዮጵያ በገልፉድ ዓለምአቀፍ ኤክስፖ ላይ መካፈል እየተቀየረ መሄድ ችሏል፤ ገልፉድ ኤክስፖ የንግድ ትርኢት ሲሆን ለኢትዮጵያ አምራቾች እና ላኪዎች የኢትዮጵያን የግብርና ምርት ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥር መድረክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ከተሳተፈችበት ዓመት ጀምሮ በየግዜ በጥራት እና በብዛት የተሻሻለ ምርት በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡

25ኛው ዓመታዊ ገልፉድ 2020 የንግድ ትርኢት “Rethinking Food” በሚል መርህ ከየካቲት 8-12, 2012 ዓ.ም በዱባይ ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያም በቀደሙት ዘጠኝ ዝግጅቶች ላይ እንደነበረው ከ130 በላይ ላኪዎች ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ የቅባት እህሎች፣ ቅመማቅመሞች፣ ቡና እና የቀንድ ከብቶች ለእይታ ከቀረቡት ውስጥ ሲሆኑ በተጨማሪም ማር ፣ ስጋ እና ታሂኒ ለእይታ ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ተሳትፎ በአምባሳደር ምስጋኑ ማሩ የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በይፋ ከፍተዋል፡፡ ዛአቤል አንድ አዳራሽ ውስጥ ሁለት የኢትዮጵያ ማሳያዎች የተዘጋጁ ሲሆን ‹‹ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት›› በሚል የተሰየመውና በኢትዮጵያ የግዕዝ ፊደላት ያጌጠው ማሳያ ውስጥ ኤክስፖውን የተካፈሉ ጎብኚዎችን ቀልብ የሳቡ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት እና ውበት ሚያሳዩ ምስሎች የቀረቡበት ነበር፤ ይህም ሁለቱን የኢትዮጵያ ማሳያዎች በበርካታ ጎብኚዎች እና ገዢዎች ለመጎብኘት እድል አስችሏቸዋል፡፡ በርካታ የውጪ ዜጎች ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ የቡና ስርዓት ላይ በመታደም እና በባህላዊ ምግቦች በመደሰት አሳልፈዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የሆነውን ጤፍ ለማስተዋወቅ በማሳያዎች ውስጥ የጤፍ ብስኩት እና ኬክም ቀርቧል፡፡

‹‹የንግድ ትርኢቱ ለኢትዮጵያ ላኪዎች እና አምራቾች ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥር መድረክ ነው ›› ያሉት በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ግ.ት.ኤ) ሲኒየር ፕሮጀክት ኦፊሰር ማህሌት መኩሪያ ናቸው፡፡ በመጨመርም ‹‹ባለፈው ዓመት የገልፉድ ተሰትፎአችን ከኢትዮጵያ ምርቶች ሽያጭ 70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተጠብቆ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት የንግድ ትርኢት ተሳትፎ 85ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ይጠበቃል›› ብለዋል፡፡

ትክክለኛውን የሽያጭ መጠን የተደረጉ የሽያጭ ስምምነቶች ላይ ጥናት ከተደረገ በኋላ ይፋ ይደረጋል፡፡

የኢትዮጵያን ምርቶች ለእይታ ከማቅረብ በተጨማሪም ከተለያዩ የኢትዮጵያን ምርት እየገዙ ካሉ እና የወደፊት ደንበኞች ሊሆኑ ከሚችሉ ድርጅቶች ጋር ውይይት እና ስብሰባ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በላይ ጉዞው ከሌሎች አገራት ጋር የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ሲሆን የዱባይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ያዘጋጀውን የቡና ማቀነባበሪያ በኢተዮጵያ የቡና ላኪ ተወካዮች ተጎብኝቷል፡፡

ይህ ኢትዮጵያን በገልፉድ 2020 የማስተዋወቅ ስራ በግብርና ንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ፕሮጀክት እና የመልቲ ሴክተራል ቴክኒካል ኮሚቴ አማካኝነት በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ትብብር አማካኝነት ስኬታማ ሊሆን ችሏል፡፡ ፡ ባለፉት አራት የገልፉድ ዝግጅቶች ላይ ግ.ት.ኤ የማሳያ ቦታዎችን ዲዛይን ከማዘጋጀት ጀምሮ ለምግብ ቅምሻ የሚሆኑ ቦታዎችን ማደራጀት ጨምሮ የገበያ እና የኮሙኒኬሽን ስራዎችን በመስራት ለንግድና ኢነዱስትሪ ሚኒስቴር ድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ግ.ት.ኤ በዚህ ዝግጅት ውስጥ ባለው ተሳትፎ ትልቁ ዓላማው ትናንሽ አርሶአደሮች ያላቸውን ምርት ከአገር ውስጥ እስከ ዓለምአቀፍ ገበያ ድረስ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር እና አርሶአደሮቹ እድሉን እንዲያገኙ ማመቻቸት ነው፡፡

Facebook
Twitter
LinkedIn